አባይ ሚዲያ ዜና በዘርይሁን ሹመቴ

በጀርመን የስደተኞች መኖሪያ በተቀሰቀሰ የእሳት አደጋ ወደ 30 የሚሆኑ ሰዎች መጎዳታቸው ታወቀ። ከተጎጂዎች ውስጥ ሁለት 2 የእሳት አደጋ ተከላካይ ሰራተኞች ይገኙበታል።

አደጋው የተከሰተው በሰሜን ራይንዌስትፋሊያ North Rhine-Westphalia ተብሎ በሚጠራው የጀርመን ክልል በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ሲሆን አንድ ሰው ክፉኛ መጎዳቱ ተጠቅሷል።

እሳቱን ለማጥፋት በጠቅላላው 100 የሚሆኑ የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ ሰራተኞች እንደተረባረቡበትም ታውቋል። ባሳለፍነው ሐሙስ በደረሰው በዚህ የእሳት ቃጠሎ የተጠረጠሩ አምስት የአከባቢው ነዋሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም መረዳት ተችሏል።

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት መገባደጃ ላይ የቱኒዚያ ስደተኛ በበርሊን የገና ገበያ ላይ ደረሰው አሰቃቂ አደጋ የ12 ሰዎች ህይወት እንዳለፈና ከ50 የሚበልጡ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል። ለዚሁ የበርሊን አደጋ የአይ ኤስ ድርጅት ሙሉ ሃላፊነቱን መውሰዱም ይታወቃል።

የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ለፈረንጆቹ አዲስ አመት በሰጡት የእንኳን አደረሳችሁ መልክት ህዝቡ በበርሊን በተከሰተው አሳዛኝ ክስተት በመነሳሳት ወደ ብቀላና አመጽ እንዳይሻገር አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው ያታወሳል።

በዚህ የስደተኛ ካምፕ የደረሰው የእሳት አደጋ ከበርሊኑ ጥቃት ጋር የተያያዘ መሆኑን ምንም አይነት መረጃ ይህ ዜና እስከ ተጠናከረበት ሰአት አልተገኘም።

የስደተኛ ካምፑ ለ500 ጥገኝነት ጠያቂ መኖሪያ እንደሆነም ተገልጿል። ስደተኞቹም በአብዛኛው ከምእራብ ባልካን አገራት የመጡ ናቸው። በስደተኞቹ መኖሪያ አደጋው ቢደርስም አሁንም ካምፑ እንዳልተዘጋና ስደተኞቹን አስጠልሎ እንደሚገኝም ተረጋግጧል።