“በነጻነት ተወልዶ በነጻነት መኖር”

“Born Free*!”

0

ለቴሊቪዥን ጣቢያ ተጨማሪ ገንዘብ የምከፍልበት አንዱ ምክንያት ለ“Animal Planet” “ቻነል” ስል ነው። ከሰው ልጆች የዕለት ተዕለት የዜና ትዕይንት ቀጥሎ ተፈጥሮን እና ፍጥረቶቿን በሰማይ፣ መሬትና ውሃ ውስጥ እንደማየት የሚመስጠኝ ትዕይንት የለም። በተለይም የንጋቱ “Big Cat Diary” … ከእንቅልፌ ስነቃ አይንና እጄ ሮጠው እዚያው ቻነል ላይ ናቸው። በ“Big Cat” ዝርያ ውስጥ የሚመደቡት አንበሳ፣ ነብር እና አቦ ሸማኔ ናቸው። በፕሮግራሙ ውስጥ የሚታዩት፣ አሳድደው ከሚይዟቸው እና አንዳንዴም የሞት እና ሽረት ትንቅንቅ ከሚገጥሟቸው ሌሎች እንሰሳት በስተቀር ሶስቱ ናቸው። በተለይ የአንበሳ ድፍረት፣ ጥበብ እና የቡድን ስልት እጅግ ይገርመኛል። አንድ አንበሳ ብቻውን ከአስር ጊዜ በላይ በክብደት የሚበልጠውን አውራሪስ ይጥላል። አንድንዴም ይወድቃል። ከሁሉም የሚያናድደኝ እና የሚያሳዝነኝ ግን አጋዥ አጥቶ በመንጋ ጅቦች ተከቦ ሲወድቅ ነው።

አንበሳ ጋር እንዲህ ያቆራኘኝ ግን፣ እንደ ጎ. አቆ. በ1950ዎቹ ውስጥ የተጻፈ፣ የዛሬ ሃያ አመት ገደማ ያነበብኩት “Born free” በሚል ርዕስ ዝናን ያተረፈ እውነተኛ የአንበሳ ታሪክ ነው።

የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ በዘገበበት ጽሁፍ ላይ ያለው የዶ/ር ብርሃኑ ዜና ጋር የወጣውን ይህን ፎቶ እንዳየሁ አይምሮየ ላይ የመጣው፣ በ“Big Cat Diary” ፕሮግራም፣ በጨለማ ውስጥ የሚያድኑት፣ አንዳንድ ጊዜም በፕሮግራሙ መሃል “ፎቶ-ገጭ” (still photography/picture) አድርገው “ቲቪ”ው ላይ ድንገት በጥቁር እና ነጭ ምስል የሚቀርጿቸው አናብስት ናቸው። አለቀ!

dr-birhanu-and-the-lioness

በተረፈ፣ በሃገር ፍቅር ስሜቱ ልዕልና፣ በሰብዓዊ የሞራል ብቃቱ እና ስለ ህይወት እና/ወይም መኖር ባለው ፍልስፍና፣ እጅግ የማደንቀው ሰው ከመሆኑ በቀር፣ ዶ/ር ብርሃኑን ሰዋዊ-አምላክ (divinize) የማድረግ ነገር አይደለም።

እንዲያውም “divinization” የኛ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ችግር እንደሆነ “ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” ከሚለው ራሱ ከጻፈው መጽሃፍ ውስጥ አለ፦ “…ብዙ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ታዛቢዎች፣ አገራችን የገጠሟትን ሁለንተናዊ የፖለቲካ ችግሮች በተለያየ ጊዜ ከተነሱ የመንግስት ስልጣን ከያዙ መሪዎች ወይንም የፖለቲካ ስልጣን ባይዙም ፖለቲካውን በተቃዋሚነት ከሚያሽከረክሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ጋር ያያይዙታል። በድፍኑ ይህ አመለካከት የሚለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመፍጠር የቸገረን ዋና ምክንያት የመንግስት ስልጣን በያዙ መሪዎችም ሆነ በተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ውስጥ ከራሳቸው የስልጣን ፍላጎት በላይ ማሰብ የማይችሉ፣ ከልባቸው ለዴሞክራሲ ያልቁሙ ግለሰቦች ባንድ መልኩ ወይም በሌላ የፖለቲካ መሪነቱ ሃላፊነት ላይ በመቀመጣቸው ነው። … ‘እንደ ማንዴላ አይነት’… መሪዎች ቢኖሩን ኖሮ እስካሁን የምንመኘውን ሥርዓት እናገኝ ነበር…” የሚል አመለካከት እንዳለን እና … “…ይህ አመለካከት በአንድ በኩል ለግለሰብ መሪዎች ከሚገባው በላይ ትልቅ ቦታ…” ከመስጠት የመነጨ መሆኑን በመጽሃፉ ውስጥ አስቀምጦታል።

እንዲያውም አብዛኛው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያን መሰረት ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ሌሎች መሪዎችን እና ቡድኖችን ከመወንጀል፣ እርስ በርስ መወነጃጀል፣ ሲያሻቸው በአንድ ግለሰብ ወይም ጥቂት የቡድን አባላቶቻቸውን ምክንያት ሲያደርጉ ዶ/ር ብርሃኑ በመጽሃፉ ውስጥ የኢትዮጵያን ችግር ያየበትን ማዕዘን የተለየ ያደርገዋል። በዚሁ መጽሃፉ ገጽ 84 ላይ፦

“…መንግስቱን እና መለስን መሸከምና አዝሎ ለረጅም ጊዜ መጓዝ የሚችሉ የመንግስት ተቋማት፣ እንዲህ አይነቱን ሥርዓት ሲፈጠርና ማህበረሰቡን እየለከፈ ሲሄድ እያዩ ምንም የማይጎረብጣቸው የማህበረሰቡ የሲቪክ ተቋማት፣ ከዕውነትና ከፍትህ ይልቅ ቁሳዊ ጥቅሙን አስልቶ ጉልበት ላለው ለጊዜው አሸናፊ አገልጋይ ሆኖ ለመኖር ህሊናው የማይወቅሰው የዕውቀትና የስነ-ጽሁፍ ልሂቅ፣ አልፎም ለተወሰነ ርቀትም ቢሆን ይህንን ሥርዓት ተሸክሞ ለመሄድ የማያቅማማ ማህበረሰብ ሲኖር ብቻ ነው…” ሲል “…የማህበረሰባችንን ታሪካዊ እና ስነልቦናዊ ሁኔታ…”ን ይጠይቃል።

Born Freeን በአጭሩ

… እንግሊዛዊው ጆርጅ እና ሚስቱ ጆይ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሌን ያዋስን በነበረው ጫካ አካባቢ ለመዝናናት ይሄዳሉ። ጫካው ውስጥ ሲዘዋወሩ ድንገት ያልጠበቁት ነገር ሆነ፤ በርቀት አንዲት አንበሳ እየተንደረደረች ወደነሱ መጣች፣ መሄጃ ማምለጫ ፈለጉ፣ ምንም መግቢያ የለም፣ ዛፍ ላይ ለመውጣት ሞከሩ፣ ጊዜ የለም፣ ወደ ሰማይ ተኩሰው አስፈራርተው ለመመለስ ሞከሩ፤ አንበሳዋ ፍጥነቷን እየጨመረች አጠገባቸው ደረሰች፣ ጆርጅ ተኩሶ መታት። እያነከሰችም ወደነሱ መገስገሷን አላቆመችም ነበር፣ ብዙ ደም ፈሰሳት። አልቻለችም። ቆመች። ከቆመችበት ሆና አንድ ጊዜ ሰዎቹን፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ኋላዋ አየች። ጠብደል ጎረምሳ ጋር ገጥሞ ሽንፈቱን መቀበል እንዳቃተው ትንሽ ልጅ በሚመስል እልህ አልፎ አልፎ ወደኋላዋ ሰዎቹን እያየች ወደመጣችበት እየተንፏቀቀች ተመለሰች። ብዙ አልሄደችም። ወደቀች። ሰዎቹ በስጋት፣ መሳሪያ እንዳቀባበሉ እና እንደደገኑ እየቀረቧት ሄዱ። ሞታለች። እጅግ አዘኑ።

በወደቀችበት አጠገብ ካለ ትልቅ ቋጥኝ ስር የአንበሳ ግልገሎች ድምጽ ሲሰሙ ነበር የባሰ ልባቸው በሃዘን የደማው፣ አንድ ሳምንት እንኳን ያልሞላቸው የሶስት ግልገሎች አራስ ነበረች። መከሩ። … እንደ አውሬ ጫካ ውስጥ ከአንበሶቹ ጋር እየኖሩ ሶስቱንም አሳድገው ሁለቱን ለሆላንድ አገር “ዙ” አሳልፈው ሰጥተው፣ አንዷን ግን እዚያው ጫካ ውስጥ እየኖሩ፣ እንደ ልጅ ያሳድጉ ጀመር። አንበሳዋን የማሳደጉ ዋና ሃላፊነት የወደቀው ከጆርጅ ሚስት (ጆይ) ላይ ነበር፣ አንበሳዋም ጆይን ትፈቅድ ነበር… ምግብ ማቅረብ፣ ማጫወት ይችላሉ፣ እያደገች ስትሄድ ግን ነጻነቷን መንሳት ሆነባቸው። እንደገና አውሬነቱን አለማምደው፣ ራሷን ችላ፣ ከሌሎች አንበሶች ጋር ማህበራዊ ህይወቷን በርቀት እያዩ፣ አድና (“ድ”ን ጠበቅ) መብላትን ራሷ እንድትለምደው አድርገው፣ በነጻነት… ወልዳ ከብዳ … መልሰው በነጻነት በዱር እንድትኖር ስላደረጓት አንዲት አንበሳ “ኤልሳ” ነው ታሪኩ–“Born Free!”

በዋሺንግቶን ዲሲ ላይ በተደረገው ስብሰባ ላይ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፦ “…ማናችሁም ህይወታችሁን እንደምትወዱት እኛም ህይወታችንን እንወዳለን፣”… እንዲያውም “ህይወታችንን በጣም ስለምንወዳት ነው የምንታገለው፣ በጣም በጣም ስለምንወዳት…ዝም ብሎ ዝም ብሎ ከመኖር በእውነት ህይወትን የምናጣጥምበት ኑሮ እንድንኖር ነው የምንታገለው፣ ህይወትን ማንም ይኖራል፣ ህይወት ማለት ከልብህ በነጻነት የምትኖርበት ህይወት ነው…” ነበር ያለው። Born Free!

“At the end, it’s not the years in your life that counts. It’s the life in your years” ያለው አብራሃም ሊንከን ነበር፤ “… በስተመጨረሻ በህይወት ያሳለፍካቸው አመታት ቁጥሮች (ብዛት) ሳይሆን፣ በአመታቱ ውስጥ ያሳለፍከው ህይወት (አይነት) ነው ከቁጥር የሚገባው” እንደማለት ይመስለኛል።

ዶ/ር ብርሃኑ በልጅነቱ ነጻነትን ፍለጋ በረሃ ገብቷል፣ ነጻነትን ፍለጋ በሰላማዊ ትግል ተሰልፎ ታስሮ፣ ተሰቃይቶ ፈትኖታል፣ አሁንም ነጻነትን ፍለጋ በረሃ ወጥቷል። የሰው ልጅ አንድ ጊዜ የሚኖራትን ህይወት በነጻነት ኖሮ በነጻነት የሚፈልገውን እያደረገ በነጻነት እንደማለፍ ያለ ጸጋ የለም። Born Free!