30 SEP 2003, BERLIN/GERMANY: Roman Herzog, Bundespraesident a.D. und Vorsitzender der Kommission, Pressekonferenz zum Abschlussbericht der CDU-Kommission "Soziale Sicherheit", Bundespressekonferenz IMAGE: 20030930-03-035 KEYWORDS: Renten-Kommission, BundesprŠsident, BPK

አባይ ሚዲያ ዜና በዘርይሁን ሹመቴ

ምስራቅና ምእራብ ጀርመን ከተዋሃዱ በሃላ የመጀመሪያው የጀርመን ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ሮማን ሄርሶግ በ82 አመታቸው አልፈዋል። ሮማን ሄርሶግ ከ1994 እስከ 1999 እኤአ ጀርመንን በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።

ሄርሶግ በ1934እኤአ በባየር ግዛት ላንድሸት በሚባል ቦታ የተወለዱ ሲሆን የሁለት ወንድ ልጆች አባት እንደነበሩም ታሪካቸው ያስረዳል። በ1970 እኤአ የፖለቲካ አለሙን የተቀላቀሉት ሄርሶግ የክርስቲያን ዲሞክራቶች ፓርቲ ወይም CDU አባል በመሆን ነበር።

ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት አገራቸውን በዳኝነት ሞያ ከ1983 እስከ 1987እኤአ አገልግለዋል። የአገሪቱዋ የፍትህ መስሪያ ቤት ዋናም በመሆንም ሰርተዋል።

ሮማን ሄርሶግ በአጠቃላይ በፖለቲካ የህይወት ጉዟቸው በጀርመን ውስጥ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥና ፍትህን ለማስረጽ የተጉ እንደነበሩም ተመስክሮላቸዋል።

ለየት ያለ ስብእና ያለውና አርቆ አሳቢ በማለት ፕሬዝዳንት ዮሃሂም ጋውክ ስለ ቀድሞ አቻቸው ተናግረዋል።

ካንስለር አንጌላ መርክል በበኩላቸው ጀርመን ትልቅና እጅግ ተወዳጅ ፕሬዝዳንቷን አጣች በማለት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

ሄርሶግን ለየት የሚያደርጋቸው በናዚ ጀርመን ለደረሰው አሰቃቂ ግፍ በይፋ በ1994እኤአ በፖላንድ ዋርሶ በአደባባይ ለአለም ይቅርታ መጠየቃቸው  ነበር።

“በጀርመን ለተፈጸመባችሁ ግፍ ሁሉ ይቅርታችሁን እጠይቃለሁ” የሚለው ንግግራቸው ስህተትን በግልጽ ማመንና ይቅርታን በአደባባይ መጠየቅ እንደሚቻል ለአለም ያሰተማረ ተግባር ነበረ።