ባለው ውዝግብ ትንሽ ነዳጅ ልጨምር (ሃይማኖት ዉዱ ፍንታ ዘብሔረ መንቖረር)

0

 

በዚሀ የፈረንጆች አዲስ ዘመን ለወገኖቸ መልካሙን ሁሉ እየተመኘሁ፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ ፕሮፌሰር ፓዉሎስ ሚኪያስ፣ እና መሪ ራስ አማን በላይ፣ በጀመሩት ውዝግብ ላይ ትንሽ ጧፍ እና ነዳጅ ልጨምርበት ተነሳሳሁ። በመሰረቱ እኔ የታሪክም ሆነ የግዕዝ ዕውቀት ሰለሌለኝ የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የጻፉት መጽሃፍ በዕርግጥ ዕውነት ወይንም ውሸት ስለመሆኑ የምለዉ ነገር የለኝም። እኔ እንዳባቶቸ እና እንደእናቶቸ ጵድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም የምል መሐይም ነኝ።

ያም ሆኖ መሪ ራስ አማን በላይ ለፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሃይሌ በሰጡት የመልስ ሃሳብ ላይ ከራስ ደጀን ተራራ የገዘፈ፡ ከአባይ ወንዝ የረዘመ፡ ታላቅ ሃቅ ስላለ፥ ምንም እንኳን ፕሮፈሰር ጌታቸም ሃይሌን ከመጠን በላይ አክብሬ የማይ ቢሆንም ይህንን ግዙፍ ሃቅ በአነስተኛ ማሰሮ ከትቸ በሶሎሞን ማህተም አትሜ አሳ አጥማጁ መጥቶ ከባህር ዉስጥ ይህንን ጂኒ የያዘ ማሰሮ እስከሚያወጣው ድረስ ከብራና መጻሃፍት የማውቃትን ብቼኛማን መልዕክተ ዮሃንስን እየደገምኩ መቆየት ባለመፈለጌ በመሪ ራስ ሃሳብ ላይ ትንሽ ለማለት ደፈርኩ። ለነገሩ ይህንን የአረቢያን ናይትእን ታሪክ አና ይህንን ጂኒ ያለ አለ አግባቡ ደንቅሬ ደግሞ ሌላ ክርክር እንዳንገባ እግዚሃብሄር ያውጣን። ወይ ጣጣ ከዳጡ ወደምጡ የሚባለው በኔ ላይ ደረሰ ለካም በእግዚሃብሄር ውስጥም ብሄር አለ።

ወደዋናው ሃሳቤ ልመለስና መሪ ራስ አማን በላይ እንዳሉት ለአለፉት ብዙ ዓመታት ማንነታችንን እየሸለሸረ ወደ እንጦረጦስ ይዞን የሚጔዝ ነገር አለ። ለነገሩ ድከም ብሎኝ ነው እንጂ ከኔ በፊት ከኔ የላቁና ከኔ በላይ የኢትዮፕያን ታሪክ ጠንቅቀው የሚይውቁ እነ ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡን የመሳሰሉ የዘመናችን ሊቆች የጳፉትን የተናገሩትን ለማንበብ እና ለመስማት ግድ ለማይለን ለእኔን መሰሎች ይህንን ሀሳብ መጻፌ ለነገሩስ ጅልነት ነው።

እስኪ ጽሁፌን ከማክሁዝ ኸርማን ልጀምር (Margaux Herman) ይህ ፈረንሳዊ የታሪክ ተመራማሪ (November 2009) ኢትዮጵያ ላይ ተደርጎ በነበረው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር አለምአቀፋዊ ፲፯ኛው ስብሰባ ላይ ሰብለወንጌል የመንግስተ ሰማየት ንግስት (Seblewengel The Queen of the the Kingdom of Heaven) የተባለ ፅሁፍ አቅርቦ ነበር። ንግስት ሰብለወንጌል ከ (1508-1540 ) በኢትዬጵያ የነገሰው የንጉሥ ልብነድንግል ባለቤት ነበረች። ይህንን የጥናት ፅሁፍ ለማንበብ የምትፈልጉ ሁሉ ዕድሜ ለጉግል ፅሁፉን በደራሲው ስም ፈልጋችሁ ልታነቡት ትችላላችሁ።

የኔ አላማ የዚችን የጎጃሙዋን ንግስት እና የመንግስተ ሰማዩን መንግስት ምንነት ለመተረክ ባለመሆኑ እዚህ ላይ ላቁምና በዚህ ፅሁፍ ውስጥ በህይወቴ ከገረመኝ አስደናቂ ነገር ልነሳ። በዚህ ፅሁፍ ገጽ ፮ ላይ ያነበበኩት ሰለ መንግስተ ሰማዩ መንግስት መደነቅን ሳይሆን እኔኑ እራሴን በልብድካም ወደ መንግስተ ሰማያት ወይም ወደ ገሃነም ያለ አድሜየ ልኮኝ ነበር። ዓሳ ጎርጉዋሪ ዘንዶ አወጣ እንደሚባለው ጉድ ሆኘ ነበር።

ጸሃፊው መረጃዎቹን ያገኘሁት ከሁለት ምንጭ ነው ይልና አንደኛው የጎጃም ታርክ የነገስታት ዘር አመጣጥ ከሚለው ተክለእየሱስ ሃተታ ነው ይልና ትንሽ ወረድ ብሎ አለቃ ተክለእየሱስ ግንደብረት እንደተወለዱና በ 1875 ተክለየሱስ ተብለው ከመጠመቃቸው በፊት ናጋሮ ዋቅጅራ (Nagaro Maqjira) ይባሉ እንደነበረና የበተክህነት ትምህርታቸውን ድጉስ ስእል በአለቃ ሳሀሉ እንደተማሩ እና በ 1920 ደብረማርቆስ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተገላገሉ ጎጃምን የተመለከቱ ጽሁፎቻቸውን ከ 1906- 1907 ባለው ግዜ እንደ አተቱ ይዘግባል። ይህ ከይሲ ፈረንጅ የአለቃ ተክለየሱስ ኦርጅናል ቅጂዎች በብሄራዊ ሙዚየም ኢትዮፕያ አንደሚገኙና ኦርጅናል የብራና ፅሁፎች ግን አሁንም ደብረማረቆስ ከተማ ነዋሪ በሆኑት በአቶ ዉዱ ፍንታ እጅ ይገኛሉ ይላል ፀሃፊው የአለቃ ተከለየሱስ መፅሐፋ ዋና አላማ በጎጃም በየደብሩና በየጎጡ የሰፈረውን የጎጃሜን የዘር ሃረግ ለማተት ነው ይላል። ይህ እኞ የአቶ ዉዱ ልጆች ብቻ ሳንሆን መላው

የጎጃም ህዝብ የዚህ ታሪክ ወራሸ መሆን በተገባው ነበር። ግን ታዲያ ይህ ኦርጂናል እና ሌሎችም የብራና ፅሁፎች የት ደረሱ፨ አባታችን ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዪ ብዙ ዘመን ተቆጠረ ታዲያ እነዚህ ታላላቅ ጎጃም ተኮር የብራና ፅሁፎችና አባታችን ለዘመናት የአጠራቀሙዋቸዉ ከአለቃ ሳህሉና ከአባታቸው ከመላከ ብርሃን ፈንታ የወረሱቸው ኦርጂናል የብራና ፅሁፎች ጨምሮ የት ደረሱ

በልጅነቴ የማስታውሰው ነገር ቢኖር ስማቸውን ጠርቶ ለመጨረስ የሚያስቸግር የጥንቱ ባህላዊ ትምህርት ቤት ምሁራን እና ዘመናዊ ምሁራን ለምርመራና ለጥናት እያሉ በጊዜው በደብረማርቆስ ብቸኛዋ ደርብ ቤታችን እየመጡ ከአባታችን የብራና ፅሁፎች ብቻ ሳይሆን ጠጅም እየቀረበላቸው ከሁለቱም ማዕዶች ዕውቀትና ጠጅ ይጎነጬ እንደነበር አስታውሳለሁ በዚህ የጠጅና የብራና ግርግር ቁጥር ስፍር የሌላቸው የንጉስ ተክለሃይማኖት ብርሌዎች እና አለቃ ተክለእየሱስን እና ባለቅነው አባታቸዉ መላከብርሃን ፋንታ የመሳሰሉ የጎጃም ታሪክ ፀሃፊዎች የፃፉዋቸው የብራና ድግሶች በማወቅ ወይንም በአለማወቅ ጠፍተው እንደሚሆን ግን መገመት አይሳነኝም

ይህንን ካልኩ በሁዋላ እስኪ መሪ ራስ አማን በላይ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ስለሰጡት መልስ ፍሬሃሳብ ልመለስ መሪ ራስ የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን መፅሐፍ አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ ላይ እንዲህ ይላሉ እኔ ግን በፊት ሌሎች ምሁራን ነን የሚሉ ሰዎች እንደዚሁ ብራናዎችን አሳየን ብለውኝ ባሳያችው ሊወስዱብኝ ሞክረው ስለነበር ከስተቴ ተምሬ ብራናዎችን ለመስጠት አልፈቀድኩም ይላሉ። ጉድና ፀፀት ከወደኁላ ነው ይባላል ምነቅ አባታችን በግዜው መሪ ራስ አማን በላይን የመሰለ ሰው አግኝተው ቢሆን ኖሮ እላለሁ አንዳንዶቹ የብራና ቅጅዎች አገር አቛርጠው በእንግሊዝ በጀርመን በአሜሪካ በተመዛግብት ተከማችተዋል። አስኪ ወደ የጥንቷ የሶቬት ግዛት ወደነበረችው አርሜኒያ ገዳማት ሂዱ ኢትዮጵያ እራሱዋ እኮ ያን ያህል የብራና መፃህፍት የላትም የኢትዮጵያ ሊቃውንት በሙሉ ስራቸውን የሰሩት እነዚህ ገዳማት ውስጥ ነው ተቀምጠዉ ነዉ የሚመስልው

ፈረንጆች (Tip of aan Iceberg) የሚሉት ነገር አላቸው የኛታሪክ እንደዚሁ ጫፉ ብቻ የሚታይ በጥልቁ ውቅያኖስ ውስጥ የተደበቀ የእውቀት ተራራ ሆኖብናልየኛ ለአለፉት ብዙ ዘመናት ማንነታችንን እየሸረሸርን የእምነትና የማንነት መግለጫ የሆኑትን ስብእናችንን ጨመረን በመቸብቸብ ላይ እንገኛለን የላሊበላን መስቀል ሳይቀር ይህ ነው በማይባል ተራ ገንዝብ ለፈረንጅ አሳልፈን እንሸጣለን። የቅኔው መምህር የመርጌታ ጥበቡ ልጅ ታላቁ የዘመናችን ኢትዬጵያዊ ምሁር ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡ አዉሮፖዉያንን ያማከለ ዕዉቀትን ምንነት ደጋግሞ አስተምሮን ነበር። እኛ ግን ጀሮ ዳባ ልበስ ብለን አዉሮፖዉያንን ያማከለ ዕዉቀትን እንደ ዕዉቀት ቆጥረን ያለእኛ ማንአለ እንላለን። አዉሮፖዉያንን ያማከለ ዕዉቀት እኛን ይለውጥ እንደሆነ እንጅ እንደ ኢትዬጵያ ያሉ ሃገራትን መለዎጥ አይችልም ከቴክኖሎዺ ባሻገር ከነጭ የምንፈልገው ምን ነገር አለ?

እራሳችንን እና ማንነታችንን ሸጠን ለዉጠን ታላላቅ የምንላቸው ምሁራን እንኳን ሳይቀሩ የኛን ሊቃውንት ከመጥቀስ ይልቅ ሸክስፒርን መጥቀስ ይቀናቸዋል። ምን ያህል ዘረኛነት በሸክስፒር ኦቴሎ እና የቬኒሱ ነጋዴ ውስጥ መኖሩን ሳንረዳ እያጎ ቃሲዬ ዲዝዲሞናን የልጆቻችን መጠሪያ ስም አድርገናል አብርሃም ሊንከን ዋሸንግተንን ስንጠቅስ ዋሸራን ግን ረስተናል። የፅሁፎቻችን መጀመሪያም ሆነ መቁዋጫ የነጭ ታሪክ ነው፤ስለነ ቢስማርክ ጆን ኦፍ አርክ ናፖሊዮን እስታሊን ማርያ ትሬዛ ስናዎራ በሃገራችን የመንግስተ ሰማያት የሚባል መንግስት ሰለመኖሩ አና ስለንግስቲቷ ሰበለወንገል ጠቅሰን አናዉቅም

በደጉ ዘመን ተፈራ ካሳ የተባለ አንድ ዘፍኝ ምን ብሎ ነበር መሰላችሁ፣

ለኛ የማይስማማ ግንጥል ጌጥ ምንድን ነዉ

ባህላችን ይበቃል ሌላ የሌላ ነዉ

መሰልጠን መሻሻል ተገቢ ነዉ በዓለም

በአዕምሮ ነዉ እንጂ በልብስ እኮ አይደለም

ለምሳሌ ህንዶች በጣም ስልጡን ናቸዉ

አልተቀላቀለም ከሌላ ባህላቸዉ

ዛሬ ብዙሃን ህንዶች እና ሲንጎች ያችኑ የባህል ልብሳቸዉን እንደለበሱ መንኮራኩር ወደ ጠፈር አምጥቀዋል። እኔና እናንተስ? እኔና እናንተ ግን ገና የፈረንጁን ልብስ ገና ሳንገዛ የአበሻ ልብሳችንን አዉልቀን መለመላችንን ቆመናል። ብርዱ እያንቀጠቀጠን አርዙን አልብሱን ተቸሩን እያልን ፈረንጅ እንለምናለን። እነሱም እግዜርን ፈርተዉ ሳይሆን የሚጥሉበት ስላጡ ዉራጅ በቦንዳ በቦንዳ ጠቅለዉ ይልኩልናል እግዜር ይስጥልን ሳንል የሚቀጥለዉ ቦንዳ መቸ ይደርሳል ብለን እንጠይቃለን። ጎበዝ እኛ እኮ ለአሁኑ ሳይሆን የዛሬ አስር አመት ይመጣል ብለን ለአሰብነዉ ርሀብ ዛሬ የልመና ማመልከቻ የምናስገባ ጉደኞች ነን።

የኞ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ መጥፎ ናቸው ብለን ደምድመናል። ለነገሩ ከመለመን እና ከነፍስይማር የሃገራችንን ደበሎ ቡሉኮ ወይንም ገሳ ብንለብስ አይሻልም ትላላችሁ? ብዙ ዘመናዊ ኢትዬጵያዊ ልጆቹን በአንቀልባ ከሚያሳዝል ራሱ በገመድ ቢሰቀል ይመርጣል። ፈረንጅ ሀገር እጅግ ብዙ ህጻናትን የሚያጠቃ የጤና ስጋት አለ። ይህን የጤና ስጋት ፈረንጅ ደቨሎፕመንታል ሂፕ ድይስፕላሲአ ይሉታል። ይህ የጤና ስጋት ግን በሐገራችን ብዙም አይታወቅም። እንዲያዉም የለም ማለት ይቻላል። ለምን መሰላችሁ በአንቀልባ ምክናያት ነዉ እኔን ካላመናችሁ ፈረንጅን ጠይቁ።

አንደርብ ጥላወጊ እኮ በፈንጅም አሉ። እስቴልት ቴክኒዎሎጅ (stealth technology) ምን መሰላችሁ? እነሂህን ፅውቀቶች በሙሉ የደብተራ ባህል ብለን ፈርጀን የአጽዋትና የዕፅ መድሃኒቶቻችንን አሽቀንትረን ጥለን ቴትራሳይክሊንና ፔኒሲሊን ለራሳችን በራሳችን እናዛለን። የአውሮፓውያን ዕውቀት ምንጭ ፈር ቀዳጆች የወጡት ከገዳማት መሆኑን ረስተን የኛን የደብተራ ባህል ብለን በአንድ ወቅት እነዚህን ሊቃውንት ማስር እና መግደል ደርሰን ነበር።

ምነው በፈረንጅ ይኸንን ያህል አመለክን? ነገሩ ወዲህ ነው። ሄግል የተባለው አዉሮፓውያን ያማከለ የምዕራቡ ዓለም የሚኩራራበትን ምእራባዊ ስልጣኔ ባህረ ሃሳብ በዋንጫ በዋንጫ እያደረገ ለነጩ ዓለም ሲያድል ለኛም በሲኒ አስር ለአንድ አቅምሶናል። ፕሮፌሰር ተሻለ እንዳለዉ ሄግል በመሠረቱ የነጩን ዓለም የዕዉቀት ካስማ ምሰሶና ማገር አስማምቶ የሰራ ብቻ ሳይሆን ያችን ፍሬደም የምትባለዋን ሞገደኛ ቃልም የፈለሰፈ ሰው ነው፤

እኛ መቸም ፍሬደም የምትባለዋን ቃል ጠርተን አይደክመንም። ጎበዝ ፍሬደም የምትባለው ቃል እኮ እኛን አትጨምርም። ሄግል የፍልስፍና ታሪክ በሚለዉ መፅሐፉ ፍሬደም የምትባለዋን ሞገደኛ ቃል ሲጠቀም እኛ እንዳንገባባት አድርጎ ነዉ። ይግረማችሁ እና የአፍሪካ በባርነት መማቀቅ የሬድ ኢንዲያኖች ዕልቂት እና ቕኝ ገዥነት የሰዉ ልጅ ፍሬደም መገለጫዎች ናቸዉ እንደ ዕርሰ ደብር ሄግል ትንንታኔ። ለምን እንዲህ አለ? ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። መልሱ አጭር ነው። ነጩ ዓለም እንደ ሄግል አባባል ሙሉ ሰው አይደለም። በሰውእና በእንስሳ መካከል የሚገኝ ፍጡር ነዉ። ስለዚህ አዉሮፖዉያንን ያማከለ የነጭና የሄግል ፓራዲግም የዘመናዊ ዓለም ታሪክ አርጎ የሚያየዉ የነጭን ታሪክ ነዉና የኛ ታሪክና ፍሬደም ፍሬደም እያልን ከነጭ ጋር ከመሟዘዝ እኛን የሚገልጡ ቃላትን ብንጠቀም ምን ይመስላችሗል። እንሟዘዝ ብንልስ ነጭ መቸ ቢሰማን። ለማስደሰት ያህል ዝም ቢሉንም ዘመናዊ ታሪክ የሌለን ሰዎች መሆናችንንና ፍሬደምም እንደማይገባን ከልባቸው ያምናሉ ለዚህ ይሆን አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት “ምን እንዳይቀርባችሁ ነዉ ያሉት” “what do you have to lose

ይህ ጉደኛ የአዉሮፓውያን የዕውቀት አድማስ ቁንጮ። ማርክስን የአስተማረ የፈረንጅ ሊቀ ጠበብት። የአለም ታሪክ ፍልስፍና በሚለዉ ሌክቸሩ እንደዚህ እያለ ይገልጸናል ጥቅሱን የወሰድኩት ከፕሮፌሰር ተቫለ ጥበቡ መጽሃፍ “Hegel and the third World. The Making of Eurocentrism in World History” መጽሃፍ ነው (page xix introduction)

“In Africa proper, man has not progressed beyond a merely sensuous existence and has found it absoulitly impossible to develop any further. Physically he exhibits great muscclar stength, which enables him to perform arduous labours and his temparament is characterized

by good-naturedness, which is coupled, however, with complitely cruelity. Asia is the land of of anthithesis, divisio, and expansion, just as Africa is the land of concentration. One pole of the antithesis is that of ethical life, the universal rational essence remains solid and substantial; the other is the exact spritual opposite, that of egoism, infinite desires, and boundless expansion of freedom in to the particular, of control of the immediate and elevation of the particular to the universal, and of the descent of the sprit into itself”

ይህንን መተርጎም ራሱ ስድብ ነው ግን በአጭሩ የሚለው አፍሪካዊ ሰው አይደለም ፍሬደም አይገባዉም ነዉ የሚለዉ። ልፉ ብሎን ሰዉ የሆንበትን የሃሳብ ዉቅያኖስ ንቀን ትተነዉ ሰዉ አይደላችሁም በተባልንበት ባሕር ካልዋኘን እንላለን። የኛ ምሁራን የዘርያይቆብን ማንነት ሳናውቅ ሄግልን ያለዉን ይዘን ፍሬደም ፍሬደም እንላለን። የዘርዓይቆብን የብራና መጻህፍትን እየቸበቸብን ለምን ሸጥከዉ ስንባል ለምርምር ነዉ እንላለን። እንዲያዉ ለነገሩ ምናለ መጀመሬያ ለስሙ እንኩዋን አንብበን ብንሸጠዉ፤ ምን አልባት እኛም እንደ ፕሮፌሰር ክላውድ ሰምነር የፈረንጅ ስማችንን ቀይረን ገላዉዲዎስ እንባል ነበር

በአሁኑ ግዜ ያለዉን ባላዉቅም ከ1953 እስከ 1969 በነበሩት ዘመናት የ ፲፪ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አልፈው ወደተለያየ ዩንቨርስቲ ከሚገቡት ተማሪዎች ከመካከል ዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ይመጡ የነበረዉ ወይ ከሸዋ ከኤርትሪያ እና ሐረርጌ ነበር ከነዚህ ዉስጥ ሃምሳ በመቶዉ ከአዲስ አበባ ነበር የአነዚህ ከሠለጠኑ አካባቢ የመጡ ወጣቶች የዕዉቀት መለኪያ እንግሊዘኛን ጠንቅቆ ማወቅ ነበር

እንደኔ እንደኔ የፕሮፌሰር ፍቅሬ መጽሐፍ ሀቅ ሆነ ሚት የኢትዬጵያን ብሔርተኝነትን የማይቃረን ከሆነ ችግሩ ምንድን ነዉ ዓለም እኮ በሚት የተሞላች ነች። ኑሯችን እምነታችን እና ማንነታችን በሙሉ ሚት ናቸዉ። ትንሽ ቆይተን ደግሞ አክሱም ያለዉን ጽላተ ሙሴ የእዉነት ወይንም የዉሸት መሆኑን እንመርምር እንዳንል። ለነገሩ የጽላተ ሙሴ መያዣ ሣጥን የተሰራበትን ነገር ወርዱን ቁመቱንና ስፍቱን በደንብ የሚገልጽ መረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለሚገኝ ምርመራዉ ምንአልባት ሊያስደስተን የሚችልበት ዕድል ቢኖርም በሌላዉ መንገድ ደግሞ በሃያ ሰኮንድ ዉስጥ የብዙ ዘመን የእምነታችን መሠረት ሊናድ ይቻላል።

ለነገሩ የእምነታችን መሠረት ቢናድ ምን ገደደን። እስኪ በኢቤይ እና በአማዞን የመገበያያ ድህረ ገጾች ላይ ታቦቶችን መስቀሎችን የብራና መጻሕፍትን ለሽያጭ ማን አዉጥቶ ለጠፋቸዉ? እኛዉ አይደለንም።

ይህ ለምን ሆነ ብላችሁ ለምትጠይቁኝ ሁለት ከበድ ያሉና አንድ ቀለል ያለ የችግሮቻችንን መንሲኤ ልጠቁምና ጵሁፌን ልቌጭ።

ለጊዜዉ ሶስት ነገሮች ልጠቁም

፩ የባህር ዛፍ

፪ የባህር ማዶ ትምህርት

፫ ስለ ራሳችን እና ስሌላዉ ዓለም ያለን ግንዛቤ ናቸዉ

የባህር ዛፍ የመጣዉ ከባሕር ማዶ ሀገር ነዉ ያዉም ከበረሃ ሀገር። ከአዉስትራሊያ። የጥንት የኢትዬጵያ ዛፎች ስሮቻቸዉ ጠልቀዉ አይሄዱም ነበር በቂ ዉሃ ስለነበረቅጠሎች ያ አስፈላጊ አልነበረም። በአንጻሩ ሐይለኛዉን ዝናብ ገድበዉ እና አቀዝቅዘዉ ወደ መሬት የሚጥሎ ሰፍፌ ጃንጥላ የመሰለ ቅጠሎች ነበሩዋቸዉ። ባህር ዛፍስ? ባህር ዛፍማ ደብረማርቆስ የተከልከው ስሩን አባይን ተሻግሮ ጎሀጽዬን ታገኘዋለህ። ቅጠሎቹስ እኛን ለመሰለ ሀገር ጥቅማቸዉ ምንድን ነዉ።

ለድርቅ በሃገራችን መከሰት አንዱ ታላቅ ምክንያት ባህር ዛፍ መሆኑን ራሳችሁ ተመራመሩና ድረሱበት አሁን እኔ ተጨማሪ መረጃ አልጨምርም የሀገሩን በሬ በሀገሩ ሰርዶ ከማለት ዉጭ።

ሌላው ነገር ደግሞ የውጭ ሃገር ትምህርት ነው ጥንታዊ ሀገር በቀሉ ትምህርት ቤት ተምሮ ለመጨረስ ከሃያና ሰላሳ ዓመት በላይ የሚፈጅ ነበረ። ብዙዎቻችን ከቆሎ ተማሪ የዘለለ ምን መሆኑን የምናውቅ አይደለንም። ፊደል መልዕክተ ዬሃንስ ዳዊት ብቻ ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት በላይ ይፈጁ ነበር። ጽጔ ጸመ ድጔ ትርጔሜን ጨምሩበት። አሮጋንን ታምረ ማርያም ታምረ እየሱሰን አትርሱ።

ይህ ብቻ ሳይሆን በቅዳሴ ቤት ደብረ ድቁና ገብረ ቅስናን ተምሮ ደበሎ ለብሶ ከሃገር ሃገር በመዞር ቅኔ ቤት ገብቶ ወርቅን ከሰም አንጥረዉ እየለዪ ጉባየ ቃናን ዘመላክን ዋዜማን ንብዙሕን ሥላሤን ዘይቤን ክብረታትን እጣነ ሞገስንና መወድስን ጠንቅቆ ማወቅን ይጠይቅ ነበር። የጎጃሙ ትምህርት ቤቶች እነጎንጅና ዋሸራማ በነዚህ ሌላ ይጨምሩባቸዉ ነበር።

ያምሁር መጽሐፍ ቤት ገብቶ አርባ ስድስት የኦሪት (የብሉይ) መጻህፍት ሃያ ስድስት የሃዲስ መጻህፍትን የሊቃዉንትንና የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች የነ ቄርሎስን ፍትሃ ነገስትን ባሕረ ሃሣብንና መነኮሳትን ተምሮ በነዚህ ሁሉ ያለፈና የኢትዬጽያን ባህል ታሪክ እና ህግጋትን የሚያዉቁ እና ጽጔ ፀመጽጔ ዝማሬ መዋሊት አቌቌም ቅዳሴና ቅኔን አልፈዉ ነበር እጅግ ጥቂቶች አራት ዓይን ለመሆን የሚበቁት። አራት ዓይናቸዉ የበራ ኢትዬጵያዉያን በጅ የሚቆጠሩ ነበሩ፤ ይህ ተማሪ ቤት እነ አቶ ሐዲስ አለማየሁ እና ከበደ ሚካኤልን የመሳሰሉ ሰዎችን ፈጥሮልን አልፏል።

ሁለተኞዉ ተማሪ ቤት ዘመናዊዉ የምንለዉ ነዉ ይኸ ተማሪ ቤት እኔንም ጨምሮ ዕልቁ መሳፍርት የሌላቸዉ ምሁራንን አፍርቷል። ባለዲግሪዉ ባለማስተርሱ ባለፒቸዲዉ እና ፕሮፌሰሩ ዕልቆ መሣፍርት ነዉ ፋብሪካ ማምረት ከሚችለው ኮካኮላ ፍትነትና ብዛት በላይ በየአመቱ በነጭ ፋብሪካ ይፈበረካሉ። ትምህርታቸው በብዛት የሚያተኩረው መግቢያየ ላይ በገለጽኩት የአውሮፓውያንን ታሪክና ስነ ልቦና ስልጣኔ እና ባህል ላይ ባማከለ ጽንሰ ሃሣብ ላይ የተመሰረተ ዕዉቀት ነዉ። በነዚህ ትምህርት ቤቶች ተመርቆ የወጣን ሰዉ ስለ ቢስማርክ ቨክስፒር ጆርጅ ዋሽንግተን ዲሞክራሲ ስለ ሊቭራልዚም ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ሁማን ራይት ወች ስለ ፈላስፎቹ ፖይታጎረስ ሄርኩለስ ፓሪሜንደስ አስካጎረስ ሶቅራጥስ ስለነ አሪስቶትል ስለሩስ ካንት ኒሸ ስለካርል ማርክስ ጠቅሶ አያባራም ስለ ጦርነት ሲያወራም ስለ ናፖሊዮን ስለጀርመን እና ስለሂትለር ስለ አንደኛዉ ዓለም ጦርነት ስለ ሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት ራሱ የተካፈለበት ያህል በጉራና በትቢት በታጀበ ቃለ አጋኖ ሲጠቅስ ሀፍረት የለዉምጎ

እነዚህ ሁሉ ዕውቀቶች ሁሉ ለኛ ምንድን ናቸዉ? በመግቢያየ ላይ ሰለጠቀስኩት ስለ አለቃ ተክለእየሱስ ዋቅጅራ መጽሐፍ ለምን ጠቅሰን አናውቅም። ለምሳሌ እኔ ራሴ ንጉሥ ተክለሃይማኖት በቆረቖሯት ከተማ በመንቖረር ተወልጀ ተክለ ቢቀር ሃይማኖት ተብየ ተሰይሜ በንጉሥ ተክለሃይማኖት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬ ስለ ንጉሥ ተክለሃይማኖት የማዉቀዉ ጥቂት ነዉ።

ከፕሮፌሰር ፍቅሬ መጽሃፍ ለኔ የተገለጠልኝ አንድ ነገር አለ። ይኸውም የኢትዬጽያ ነገሥታት ከብዙ ማህበረ ሰብ የመጡ መሆናቸውን ነው ይኸማ በአለቃ ተክለየሱስ እና እሳቸዉን ጠቅሰው በጻፉ ሃተታ ውስጥ ይገኛል። ለምሳሌ አንዱን ልጥቀስ።

“በሗላ ልጅ እያሱ ነገሰ ያንግዜ 1604 ነበር አጼ እዮአስ ከነገሠ በሗላ እናቱ ወይዘሮ ውቢት ተገለጠች ኮራች እቴጌነት ተመኘች። አማትና ምራት ሳይገኝ መሬት የተባለው ታሪክ ደርሶ ከተጌ ምንትዋብ ጋር ዐይንና አፈር ሆኑ። ጠባቸው በረታ ወይዘሮ ዉቢት ወደሰዎቿ ወሎ ላከች። ጠብ ሲነሣ የሚጠብቅ 1200 ፈረሰኞ 6000 እግረኛ ጋላ መጥቶ ጎንደር ሰፈረ ይህም ሆኖ አልላላም። መንግስት ሊፈርሰ ደረሰ። የእቴጌ ምንትዋብ ጭፍሮች ንጉሱን አጼ እዬአስን ሊዎጉት ንጉሡም የእናቱን ወገኖች ልቦንና ደምሌን ልኮ አስመጣ። እነርሱም ሲመጡ ሺህ ሽህ ፈረሰኛ ሆነው ነው የመጡ። ጎንደርን ጋላ ሞላው። ንግግሩም ጋልኛ ብቻ ሆነ። ንጉሱ አጼ እዬአስ ሲጨንቀዉ ምክር አዋቂ ጀግና ሥዑል ሚካኤል የሚባል ከትግሬ አምጥቶ ራስ ሚካኤል በሎ ሾመዉ” ይሉናል።

ታዲያ ተባብሮ ሃገር መግዛት ሌላ ምን ትርጉም አለዉ ጎበዝ የኢትዬጵያ ነገስታት ታሪክ እኮ እኛ ዘመናዊያን እንደምንዘምረው አይደለም። በተለይ የሶስት ማህበረሰብ ባላባቶች አማራ ኦሮሞና ትግሬ እኛን ኣባት የሌለንን አማራ ኦሮሞና ትግሬ ተደባልቀውና ተደበላልቀው ገዝተውናል የአለቃ ተክለእየሱስ ዋቅጅራን የጎጃም ትውልድ ከአባይ እስከ አባይ ያነበበ ጎጃሜ በየትኛውም ነጻ አዉጭ ድርጅት የመሪነቱን ቦታ የሚያስጨብጠው የዘር ሃርግ አለው

ለዚህ አሁን ለደረስንበት ባዶነት መንገዱን ጠርጎ ወደ አዘቅት የገፋን የዘመናዊ ትምህርት የምንለው ነው በድሮ ግዜ የማይታረቅ ቅራኔ የሚባል ነገር አልነበረም ይህንን እኛ ዘመናዊያን አዋርደንና አውርደን የጣልነውን በተመለከተ ፕሮፌሰር ተሻለ እንዲህ ይላል

Quite ironically the old dydtem that the revolution overthrow does not have a paradigm of irreconsailable differences MEHERET (pardon) and EREQ (reconsilation) were the moral strucures of the old political universe

የሀገር በቀሉ ጥንታዊያን መሁራን ሃገራቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ነበሩ። በዘመናችን እንኩዋን እንደ ሃዲስ አለማየሁ፣ ማሀተመሥላሴ ወልደመስቀልን፣ አቤ ጉበኛን፣ ዬፍታሂ ንጉሤን፣ ፀጋየ ገብረመድህንን፣ ከበደ ሚካኤልን የመሳሰሉ ታላላቅ ምሁራንን ያገኘነው ከዚህ ተማሪ ቤት ነው። ያን ትውልደና የኛን ትውልድ በንጽጽር አይቶ ፕሮፌሰር ተሻለ እንዲህ ይላል ለምሳሌ ጠላት የሚለውን ቃል እኛና እነሱ እንዴት አንደምንጠቀምበት ነው። አቶ ሃዲስ አለማየሁ ህይወታቸውን አስመልክቶ በጻፍት ትዝታ በተባለው ታሪካዊ መጣጥፍ እንዲህ ይሉናል። የኢትዮጽያ ንጉሠነገሥት ሠራዊት ማይጨው ላይ በፋሺስት የጠላት ወታደር ሲሸነፍ አጼ ሃይለሥላሤ ወደ አውሮፓ እንዲሄዱና የኢትዮፕያ ተጠባባቂ መንግስት መቀመጫ ግን ወደ ጎሬ ተዛውሮ ነበር። እንደ አቶ ሃዲስ አባባል በራስ እምሩ የሚመራው ተጠባባቂ መንግስት ወደ ጎሬ እንዲዛወር መደረጉ ጎሬ በጫካ የተሸፈነ ስለነበር ከጣልያን አውሮፕላን ድብደባ ለመዳን ነበር። ሆኖም ብዙ የአካባቢው ባላባቶች እና የአካባቢው ህዝብ የንጉሠነገሥቱን ሰራዊት ለመርዳት ፈቃደኛ አልነበሩም። ይባስ ብሎ ብዙ ባላባቶች የጣሊያንን ሰራዊት ተቀላቀሉ። ይህ እጅግ አሳዛኝ ነገር ነበር ይህም ሆኖ ግን አቶ ሃዲስ በመፃሐፍቸው ውስጥ በአንድም ቦታ ከሃዲ ባንዳ ብለው ስም አላወጡላቸውም። ይህ ነበር የጥንቱ ኢትዮጵያዊነት።

እስኪ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ የጻፉትን የታሪክ ማስታወሻ እንመልከት። በዚህ መጽሐፍ እንዴት ከማይጨዉ የሸሸው የንጉሠነገሥቱ ሰራዊት በራያና አዘቦ ሰው እንደተገደለ ዘግበዋል። እንዲያውም ማይጨዉ በጦርነት ከሞተው የሰው ቁጥር በራያና አዘቦ የተገደለው ሰው ይበዛ ነበር። ይህም ሆኖ ደጅአዝማች ከበደ በየትኛውም ቦታ መጽሃፉ ውስጥ ሰው በክህደት አልከሰሱም።

ግን ለምን ብለን ብንጠይቅ ሁለቱ ምሁራን ደጃች ከበደና አቶ ሃዲስ ከጥንታዊው የኢትዮጵያ ባህል ሀይቅ የፈለቁ ሃላፊነተና መከባበር የሚለውን ጥንታዊ የኢትዮጵያ ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ ነበሩ። በሰው ላይ መሳቀና መሳለቅ ባህል ባለመሆኑ ነበር።

እኛሳ? እኛማ እርስ በእርሳችን በጠላትነት ተፈራርጀን ሳንጃ ለሳንጃ ተሞሻልቀናል። እራሳችንን የምንፈልገው ሁል ግዜ ባእድ ሃገር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ራሳችንን ፈልገን አናውቅም። ራሳችንን ፍለጋ በውጭ ሃገር ስንማስን ናሺናል ኵየሽን የሚል ነገር አገኘን። ሃገር ቤት ይዘነዉ መጣንና የብሄር ጥያቄ ብለን ተረጎምነው። ደግነቱ ተስፋ ገብረሥላሤ ዘብሄረ ቡልጋ እና አፈወርቅ ገብረየሱስ ዘብሄረ ዘጌ አልሰሙንም ሞተዋል። እኛ ግን ከመቃብር አውጥተን ለሁለተኛ ግዜ ቀበርናቸው። በነጭ ዓለም ስንጔጔዝ ናሺናሊቲ የሚል ቃል አገኘንና ዜጋ ብለን ተረጎምነው። ዜጋ እኮ ትርጉሙ ሌላ ነዉ። ዘመናዊ ምሁራን ችግራችን ኩረጃ ነው ወገኖቸ ማደግ የምንችለው አኮ የምንሰራውን ሁሉ በኢትዮጵያ ፍላጎት እና የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሰናጣጣም ነው። ማጣጣም ብቻ ሳይሆን በዚያ መሰረት ላይ የኢትዮጵያ ባህል ታሪክ ማህበረሰብ ሃይማኖት የመሳሰሉትን ነገሮች ስንቀምር ነው።

እንግዲህ እንደጀመርኩት ነዳጀን በጀመርኩት ሃሳብ ላይ ልርጭና የያዝኩትን ጧፍ ለምሁራን ልስጥ። እስኪ ምሁራን ይችን ጉዳይ ፍቱልኝ። በቀደሙ የሒብሩ የኦሪት መጽሐፍ ላይ በኦሪት

ዘፍጥረት ላይ ጌታ ሰውን ከመሬት አፋር ፈጠረዉ ይላል እኛ ደገሞ ጌታ ሰውን ከመሬት አፈር ፈጠረዉ እንላለን። በኛም ሆነ በሂብሩው መጽሐፈ ኦሪት አፍር ወይንም አፈር በኛ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። ወደ እንግሊዘኛ ደስት(dust) ብላችሁ እንዳትተረጉሙት አደራ። ሳይንስ ደግሞ ሰው የተገኘው አፋር ነው ይለናል። እንዴት ነው ምሁራን። ሳይንስና መለኮታዊዉ የፍጥረት መገኛ ኢትዮጽያ ሆነች ማለት ነው? የዚህ መልስ ከተገኘ እኮ `ምሁራኖቻችን ብቻ ሳይሆን ሳይንስና መለኮታዊው ታረኩ ተስማሙ ማለት ነዉ።

ይህንን ታሪክ ባታምኑበትም እስኪ ለኢትዮጽያዊ ብሄርተኝነት ስንል እንስማማና ሚት እንፍጠር። ሚት እኮ ጥሩ ነገር ነዉ። ሚት ማለት እንደ ግሪክ አምላክ እንደ ጃነስ ባለሁለት ፊት ነው አንዱ ፊት መጭውን የሚያይ ሲሆን አንደኛው ደግሞ የአለፈውን የሚያየው ነው

ብሄርተኝነት እኮ ያለ ሚት ብቻዉን አይኖርም። ለዚህ መለኝ ናሬን የተባለ የብሄርተኝነትን ጽንሰ ሀሣብ ተንታኝ ነጭ የሚከተለዉን ያለዉ።

nationalism can in this sense be pictured as like the old Roman god, Janus, who stood above gateways with one face looking forward and one backwards. Thus does nationalism stand over the passage to modernity, for human society. As human kind is forced through its strait doorway, it must look desperately back into the past, to gather strength wherever it can be found for the ordeal of ‘development.

መልካም ገና!